የሀገር ውስጥ ዜና

አፋሕድ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳ አስረከበ

By Hailemaryam Tegegn

February 05, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አመራርና አባላት ሊታዩልን ይገባል ያሏቸውን አጀንዳዎች ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክበዋል፡፡

በአማራ ክልል ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የአፋሕድ አመራርና አባላት በቅርቡ የሠላም አማራጭን በመከተል ከክልሉ መንግሥት ጋር የሠላም ስምምነት መፈፀማቸው ይታወሳል።

የድርጅቱ አመራርና አባላት ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በዛሬው ዕለት የተወያየ ሲሆን፥ ኮሚሽኑ የሚያከናወናቸውን ተግባራት በተመለከተ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርአያ (ፕ/ር) በዚሁ ወቅት፥ በአማራ ክልል የተከናወነውን የምክክር ሂደት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ነፍጥ አሸናፊና ተሸናፊን የሚፈጥር እንጂ ሀገራዊ መግባባትን የሚያሰፍን እንዳልሆነ የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፥ ሀገራዊ መግባባት የሚሰፍነው ሁሉም አካላት ስለሀገራቸው ለመመካከር ባላቸው ፅኑ ፍላጎት እንደሆነ አስገዝንበዋል፡፡

ተሳታፊዎቹ ነፍጥ አንስተው ወደ ጫካ ያስገቧቸውን ጉዳዮች ጨምሮ ክልላዊና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አጀንዳዎች አደራጅተው ለኮሚሽኑ አስረክበዋል፡፡

በወንድሙ አዱኛ