አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተሰራው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ የአርሶ አደሩ የመበልጸግ ሂደት ላይ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን እሸቱ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት፤ የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ በተጨባጭ ቀይሯል፡፡
በክልሉ በሚገኙ በሀዲያ፣ ስልጤ፣ ሃላባ እና ከንባታ ዞኖች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቪ አማካኝነት የገጠር ኮሪደር ልማት በአርሶ አደሮች መንደር መገንባቱን አስታውሰዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት ዋነኛ ዓለማው የአርሶ አደሩን አኗኗር ለማዘመንና ለማሻሻል ታሳቢ በማድረግ መሰራቱን አብራርተዋል፡፡
የገጠር ኮሪደር ልማት በአርሶ አደሩ መካከል የመልማት፣ የማደግ እና የመበልጸግ ሂደት ላይ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ ከእንሰሳት ጋር አብሮ ከሚኖርበት የአኗኗር ዘይቤ በመውጣት በዘመናዊ መንገድ የራሱ እና የእንሰሳት መኖሪያን በመለየት ኑሮውን ማሻሻሉን ጠቁመዋል፡፡
አርሶ አደሩ አሁን ላይ በሶላር የመብራት ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፤ ልጆቹ መብራት ማግኘት በመቻላቸው ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በጓሮው በሚያመርታቸው አትክልቶች የአመጋገብ ሥርዓቱ መለወጡን ጠቁመው፤ በእንስሳት እርባታም የተሻሻለ ዝርያ ያላቸውን በማርባት ምርታማነቱ ጨምሯል ብለዋል።
የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራው አርሶ አደሩ ትራንስፖርት ፍለጋ ረዥም ጉዞ እንዳይሄድ እና ሰዓቱን በአግባቡ እንዲጠቀም አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
አርሶ አደሩ ምርቱን ከህገ ወጥ ደላላ በመከላከል በቀጥታ ለገበያ በማቅረብ ካለአስፈላጊ ወጪና እንግልት በመዳን ገቢውን እንዲያሳድግ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡
የጤና፣ የትምህርት እና የግብርና ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ አስፈላጊውን ግብዓት ለማቅረብና ለማሟላት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡
የተጀመረው የገጠር ኮሪደር ልማት መንግሥት ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋጋጥ ከሚሰራቸው ሥራዎች አንዱ በመሆኑ በተወሰኑ መንደሮች ብቻ ተሰርቶ እንደማይቆም ገልጸዋል፡፡
የመላው የገጠሩን ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤና ሕይወት በመቀየር በሁሉም መስኮች የመበልጸግ ግብን ለማሳካት ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ