አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) አጀንዳውን ማቅረቡ በጫካ ለሚገኙ የታጠቁ ኃይሎች ትምህርት የሚሆን ነው አለ፡፡
በቅርቡ የሰላም አማራጭን ተቀብለው የሰላም ስምምነት የፈጸሙት የአፋሕድ አመራሮችና አባላት ከምክክር ኮሚሽኑ ጋር በመወያየት አጀንዳቸውን አስረክበዋል፡፡
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መሥፍን አርዓያ (ፕ/ር) ውይይቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፥ አፋሕድ ያቀረባቸው አጀንዳዎች የኮሚሽኑን አሳታፊነትና አካታችነት የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጫካ ከሚገኙ ታጣቂ አካላት ጋር በሀገራዊ ምክክር ጉዳዮች ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን አስታውሰው፥ በቀጣይም በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብና የተሳታፊ ልየታ ምክክር ለማካሄድ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የአጀንዳ ቀረጻ በማከናወንና በሚቀጥሉት ሳምንታት የአወያይ ስልጠናን በማስጀመር ለዋናው ሀገራዊ ጉባኤ የሚያስፈልጉ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል፡፡
አፋሕድ ያቀረባቸው አጀንዳዎች ከዚህ ቀደም ሲደረጉ የቆዩ ጥረቶች ውጤት ሲሆን፥ ለሌሎች ታጣቂዎችም ትምህርት እንደሚሆን ነው የተገለጸው፡፡
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራሮች በበኩላቸው፥ በሰላም ስምምነቱ መነሻነት ከዚህ ቀደም ለትጥቅ ትግል መነሻ ነበሩ ያሏቸውን አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም የተሳሳተ ትርክትን ለማረምና በጋራ ምክክር መግባባትን ለመፍጠር የሚያስችሉ እንዲሁም የሕገመንግስትና ተያያዥ ጉዳዮች የተካተቱባቸውን አጀንዳዎች በማደራጀት ለኮሚሽኑ አስረክበናል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡