አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ የተለያዩ ባለድርሻ አጋር አካላትን በማሳተፍ 2 ነጥብ 23 ቢሊየን ብር ኃብት ማሰባሰብ ተችሏል አሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።
የአስተዳደሩ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ እየካሄደ ይገኛል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በጉባኤው ባቀረቡት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለትምህርት ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት በተከናወኑ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከግማሽ በላይ ያመጡ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ 95 በመቶ እንዲሁም የ8ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከግማሽ በላይ ያመጡ ተማሪዎች ወደ 88 ነጥብ 8 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ከግማሽ በላይ ያመጡ ተማሪዎች በ2013 ዓ.ም ከነበረበት 25 ነጥብ 45 በመቶ በአሁን ወቅት ወደ 31 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል።
በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች መካከል የነበረውን የውጤት ልዩነት በማቀራረብ ረገድም ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
የትምህርት ተሣትፎና ፍትሐዊነት በማሳደግ በዕውቀትና በሥነ-ምግባር የታነፀ ትውልድን ለማፍራት ከቅድመ 1ኛ ደረጃ እስከ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት አጠቃላይ ተማሪ ቅበላ ወደ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ከፍ እንዲል መደረጉን ጠቅሰዋል።
በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በተሰራ ሥራ ባለድርሻዎችን በማሳተፍ በድምሩ 1 ነጥብ 32 ቢሊየን ለመሰብሰብ ታቅዶ አሁን ላይ ባለው ክንውን 2 ነጥብ 23 ቢሊየን ብር ኃብት ማሰባሰብ ተችሏል ነው ያሉት።
ከዚህ በተጨማሪ በተማሪዎች ምገባ ከ940 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ እንዲመገቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የተማሪ ዩኒፎርም፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና የመምህራን ጋወን በወቅቱ እንዲደርሳቸው በማድረግ በኢኮኖሚ ጫና ምክንያት የሚከሰተውን የትምህርት ማቋረጥና የክፍል መድገም መጠንን መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።