አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጸጋዎቻችንን ወደ ብልጽግና በመቀየር ረገድ የተጀመረው የሥራ ባህል ኢትዮጵያን ወደሚመጥን ከፍታ የሚያሸጋግር ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ ተፈጥሮ በልግስናዋ የውበት ካባ ላለበሰችው፣ ታሪክ በክብር ጌጥ ለኳለችው ደቡብ ወሎ፤ በ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት የተገነባው የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ዛሬ ተመርቋል።
ይህ ስፍራ የአብሮነት፣ የፍቅር እና የመቻቻል ተምሳሌት ለሆነው የወሎ ሕዝብ ተጨማሪ አዲስ የቱሪዝም ድምቀትና የልማት ዐቅም እንደሆነም አንስተዋል።
ሪዞርቱ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የቱሪዝም ኃብት በልማት የሚገልጥ እና ለዓለም የሚያሳይ መስታወት ጭምር መሆኑን ገልጸው÷ ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የንግድና የአገልግሎት እንቅስቃሴውን በማነቃቃት፣ ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ተደማሪ ጉልበት ይሆናል ብለዋል፡፡
እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ባሕላዊ፣ ሐይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መዳረሻዎችን ለሚጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች እንደ ዋነኛ መሸጋገሪያና መገናኛ ኮሪደር ሆኖ የሚያገለግል ሪዞርት መሆኑን አውስተዋል፡፡
ተፈጥሮ እና ታሪክ የለገሱንን ጸጋዎቻችንን ወደ ብልጽግና በመቀየር ረገድ የጀመርነው የሥራ ባህል ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ስኬት ብሎም ወደሚመጥናት ከፍታ ማሸጋገሩን ይቀጥላል ነው ያሉት።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐሳብ አመንጪነት በየአካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም ዐቅሞችን በመግለጥ፣ ከሕዝብ ጋር በስኬት ላይ ስኬት በመደረብ፣ ለላቀ ድል ከሚደረገው ትጋት ለአፍታ አንዝልም ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡