አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐይቅ እስጢፋኖስ ያሉት የዕውቀት ምስጢራት እንደ ሐይቁ ጥልቀት፤ እንደ ደሴቱ ጽናት ያላቸው ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በአማራ ክልል ከጎርጎራ በመቀጠል የ’ገበታ’ ውጥን ሁለተኛ ፕሮጀክት የሆነውን ሎጎ ሐይቅ ሪዞርት መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የጣና ሐይቅ ገዳማት ታሪክ ጠገብ አብያተ ክርስቲያናት እና መጽሐፍት ያሉበት አካባቢ በመሆኑ እነዚህን ሃብቶች ገልጦ ለማሳየት የጎርጎራ ፕሮጀክት አስፈላጊ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በ10ኛው ክፍለ ዘመን አርመኖች በገጠማቸው ውጊያ ከሀገራቸው ተሰደው ኢትዮጵያ ሲመጡ ያረፉት በሐይቅ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሁሉም አቅጣጫ ሰላም እና ፍቅር ፍለጋ ወደ ሐይቅ ያቀኑ ኢትዮጵያዊያን የጸኑበት ስፍራ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ክርስትና እና እስልምና ተዋደው እና ተከባብረው የሚኖሩበት ድንቅ አከባቢ መሆኑን ገልጸው÷ የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ደግሞ የስፍራው ታላቅ ሃብት መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ይህ ገዳም ስራን፣ ትምህርትን እና ጾምን በማስተማር ለትወልድ ታላቅ አበርክቶ መስጠቱን ነው ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ይህ ስምንት መቶ ዓመታትን የተሻገረ ድንቅ ታሪክ ለዓለም ለማሳወቅ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት አይነት መሰረተ ልማቶች በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ይህ እምቅ ታሪክ ያለው አካባቢ በቂ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ እምብዛም ሳይታወቅ መቆየቱን ጠቁመው÷ ይህን ሃብት ለመግለጥ የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየአካባቢዎቹ ከታሪክ ባለፈ ታሪክ ገላጭ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በአቤል ነዋይ