ቢዝነስ

ቀርጫንሼ ግሩፕ ከብራዚል የእርሻ ምርምር ተቋም ጋር በጋራ ለመስራት ተስማማ

By Yonas Getnet

February 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የቡና ኢንቨስትመንት የተሰማራው ቀርጫንሼ ግሩፕ እና በብራዚል የእርሻ ምርምር የሚሰራው ኢምብሬፓ በቡና ልማትና ተያያዥ የግብርና ስራዎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።

በፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ኢፋ ሙለታ (ዶ/ር) እንዳሉት÷ ስምምነቱ ለሀገራችን ኢኮኖሚያዊ እድገት የላቀ ሚና አለው።

ስምምነቱ ወደ ትግበራ እንዲገባና ውጤት እንዲያመጣ መንግሥት ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የቀርጫንሼ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ እስራኤል ደገፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያና ብራዚል በግብርናው ዘርፍ በርካታ የሚያመሳስላቸው ጉዳይ እንዳላቸው ገልጸዋል።

በተደረገው የስምምነት ማዕቀፍ ከብራዚል ጋር ትብብሩን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ እንዲሁም የብራዚልን የእርሻ ልማት ልምድ በተለይ የቡና ልማትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ አብረው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

በምዕራብ ጉጂ አባያ ወረዳ ደበቃ የቡና ልማት በተፈረመው በዚህ ስምምነት መሰረት በግብርና ጥራትና ቁጥጥር፣ በሰራተኞች አቅም ግንባታና ተያያዥ መስኮች ሁለቱ ተቋማት አብረው እንደሚሰሩ ተመላክቷል።

በዓለምሰገድ አሳዬ