ቢዝነስ

የኢትዮጵያን ሀብት ለማስተዋወቅ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት

By Yonas Getnet

February 07, 2026

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 15ኛው የኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቱ የኢትዮጵያን ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ቁልፍ ሚና ይጫወታል አሉ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ቀነኒሳ አለሜ (ዶ/ር)።

የንግድ ትርኢቱ የቢዝነስ አቻ ለአቻ ውይይት፣ የእውቅናና ሽልማት ማጠቃለያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡

ቀነኒሳ አለሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ ምርቶችና አገልግሎቶች በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲተዋወቁ ያስችላል፡፡

ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቱ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያግዝ እንደሆነና የኢትዮጵያ ነጋዴዎች ተወዳዳሪነትና አቅም እንዲሻሻል እንደሚረዳ ተናግረዋል፡፡

በመድረኩ በማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስ፣ አውቶሞቲቭ እና በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን ይዘው መቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡

የንግድ ትርኢቱ የሀገር ውስጥ ኩባንያዎችን አቅም ለማሳደግ እና አዳዲስ ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስሮችን ለመፍጠር የሚረዳ ዕድል ይዞ መምጣቱንም አመልክተዋል።

ትርኢቱ የግሉን ዘርፍ አቅም ከመገንባት ባለፈ የወጪ ንግድን ለማሳደግና የኢትዮጵያን ሀብት ለዓለም ለማስተዋወቅ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል።

በመርሐ ግብሩ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ የኩባንያ ባለቤቶችና ተወካዮች እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

15ኛው ኢትዮ-ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢት “የኢትዮጵያን ይግዙ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያድርጉ” በሚል መሪ ሐሳብ ከጥር 27 ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

በየሻምበል ምህረት