አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ጤና ቢሮ በክልሉ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሚሰጠውን የእናቶች ህክምና አገልግሎት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ ነው አለ።
ቢሮው “ፈጠራና ዘላቂ ፋይናንስ ለጤናማ እናትነት” በሚል መሪ ሀሳብ የተከበረውን ጤናማ የእናትነት ወር ማጠቃለያ መርሐ ግብር በጎንደር ከተማ አካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የቢሮው ምክትል ኃላፊ አበበ ተምትሜ እንዳሉት÷ በክልሉ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የእናቶች ሞት ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች ትርጉም ያለው ውጤት ማምጣታቸው በጥናት ተረጋግጧል።
ለእናቶችን የሚሰጠውን የህክምና አገልግሎት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ከ300 ሺህ በላይ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ተደርጓል ነው ያሉት።
በ322 ጤና ተቋማት ለእናቶች የአልትራሳወንድ አገልግሎት መሰጠቱን ጠቅሰው፤ በ37 ጤና ጣቢያዎች የእናቶች ቀዶ ህክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው ብለዋል።
በወሊድ ወቅት የደም መፍሰስ የሚያስከትለውን ሞት ለመቀነስም ከደም ባንኮች ጋር በቅርበት በመስራት በስድስት ወራት ውስጥ 44 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ተናግረዋል።
የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ብርቱካን ሲሳይ በበኩላቸው፤ ከቅድመ ወሊድ እስከ ድህረ ወሊድ ባሉት ጊዚያት የእናቶች ሞት እንዳይከሰት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በምናለ አየነው