አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ላለፉት ሦስት ቀናት በሰመራ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የአፋር ክልል ምክር ቤት 9ኛ መደበኛ ጉባዔ በዛሬው ዕለት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቅቋል።
በጉባዔው ማጠቃለያ ላይ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙሳ አብዶ ያቀረቧቸውን የ28 ዳኞች የሹመት ጥያቄ ምክር ቤቱ መርምሮ ያፀደቀ ሲሆን÷ ተሿሚዎቹም ቃለ መሐላ ፈፅመዋል።
ከተሿሚዎቹ መካከል ሶስት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ 12 ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲሁም 13 ዳኞች ለወረዳ ፍርድ ቤቶች የተመደቡ መሆናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም በተቋማዊ አደረጃጀት ላይ ማሻሻያ በማድረግ ቀደም ሲል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ተብሎ ይጠራ የነበረውን ተቋም ወደ አፋር ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ እንዲቀየር ወስኗል።