የሀገር ውስጥ ዜና

በግንባታ ላይ የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው

By Melaku Gedif

February 09, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተለያዩ አካባቢዎች በግንባታ ላይ የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፡፡

በባለሥልጣኑ የኤሮድሮም ሴፍቲና ስታንዳርድ ዳይሬክተር ምስራቅ ጥላሁን ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ በኢትዮጵያ ያለውን የአየር ትራንስፖርት ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም መሰረት የተለያየ መጠን ያላቸው የአውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባቱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ግዙፉን የቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ሳይጨምር በተለያዩ አካባቢዎች አምስት የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያዎቹ ግንባታ በሚዛን አማን፣ ጎሬ መቱ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ነጌሌ ቦረና እና ወላይታ ሶዶ ነው እየተከናወነ የሚገኘው፡፡

ከእነዚህ ውስጥም ሚዛን አማን እና ጎሬ መቱ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ግንባታ ከ80 በመቶ በላይ ደርሷል ያሉት ወ/ሮ ምስራቅ ÷ በቅርቡ ተጠናቅቀው ወደ ኦፕሬሽን እንደሚገቡ አመልክተዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያዎቹ ግንባታ በተለያየ ምክንያት መዘግየቱን ጠቅሰው÷ለአብነትም የአቅርቦት ችግር፣ የኮንትራክተሮች የአፈጻጸም ማነስ እና ሌሎች ምክንያቶችን አንስተዋል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡

የአየር ትራንስፖርትን ማስፋፋት የቱሪዝም ተደራሽነትን ለማጠናከር፣ ኢንቨስትመንትን ለማሳለጥና የአካባቢዎችን ዕምቅ ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል፡፡

ነቀምቴ እና ያቤሎ አውሮፕላን ማረፊያዎች በቅርቡ ወደ ኦፕሬሽን መግባታቸው ያስታወሱት ዳይሬክተሯ ÷ አሁን ላይ በአጠቃላይ 24 አውሮፕላን ማረፊያዎች እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥም አራቱ ማለትም አዲስ አበባ፣ ባሕር ዳር፣ መቀለ እና ድሬዳዋ አውሮፕላን ማረፊያዎች በሲቪል አቪዬሽን ሰርተፊኬት አግኝተው ዓለም አቀፍ በረራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ