የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት ከኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጋር ተቀራርቦ ይሰራል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Adimasu Aragawu

February 09, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት ከኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ይሰራል አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች አዲስ ከተመረጡት የካውንስሉ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የሃይማኖት አባቶች፣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተከናወነው የካውንስሉ 5ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተሳካ መልኩ በመካሄዱ ለካውንስሉ አመራሮች አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል።

መንግሥት ከኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አመራሮች ጋር በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ይበልጥ ተቀራርቦ የሚሠራ መሆኑን ገልጸው÷ በሚያስፈልገው ሁሉ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ነው ያሉት።

ለካውንስሉ አመራሮች መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸውም ምኞታቸውን ገልጸዋል።