አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰው አልባ ፖሊስ አገልግሎት የተቋሙ አገልግሎትን ዲጂታላይዝ የማድረግና ሕብረተሰቡ በነፃነት ምንም ዓይነት ጫና ሳይደርስበት በቀላሉ የሚፈልገውን መረጃ ለፖሊስ ማድረስ የሚችልበት ስርዓት ነው አሉ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰው አልባ ፖሊስ አገልግሎት ወይም ስማርት ፖሊስ አገልግሎት ስራ አስጀምረዋል።
አገልግሎቱን አስመልክቶ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በሰጡት አስተያየት÷ ምንም ዓይነት የሰው ንኪኪ ሳይኖር ተገልጋዩ በቀላሉ አገልግሎት የሚያገኝበት ስርዓት እስካሁን በውስን ሀገራት መኖሩን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ያስጀመረችው ሰው አልባ ፖሊስ አገልግሎት በአፍሪካ የመጀመሪያ እንዲሁም በዓለም አራተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህም የፖሊስን ስራ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ ገልጸው÷ የስራውን ውጤታማነት እንደሚጨምር፣ ሕብረተሰቡ ጋር ግልጽነትን እንደሚያሰፍን፣ ፖሊስ ፈጣን ርምጃን እንዲወስድ እንደሚረዳ እንዲሁም የወንጀል መከላከል ስራውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።
አገልግሎቱ በኢትዮጵያ መጀመር ትልቅ ውጤት እንደሆነና ፖሊስ ሀገሪቱ የጀመረችውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ጉዞን በማገዝ ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
በቀጣይ ሕብረተሰቡ የሰው አልባ ፖሊስ አገልግሎትን በስልኩ ላይ ማግኘት የሚችልበትን ስርዓት ለመፍጠር ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
ይህም ሕብረተሰቡ ወደ ተቋሙ መምጣት ሳይጠበቅበት በስልኩ ላይ አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚያስችል አብራርተዋል።
በአድማሱ አራጋው