የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል

By Hailemaryam Tegegn

February 10, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ነገ እና ከነገ በስቲያ ይካሄዳል

“ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሚካሄደው ስብሰባ የሚሳተፉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

በዚህም የሶማሊያ፣ የሴራሊዮን፣ የሳህራዊ ዲሞክራቲክ ዐረብ ሪፐብሊክ እና የሞሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

እንዲሁም በትናንትናው ዕለት የናይጀሪያ፣ የማላዊ፣ የኮትዲቯር፣ የቡሩንዲ፣ የኮንጎ ሪፐብሊክና የዛምቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል።

የሚኒስትሮች የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

በስብሰባው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ለመሳተፍ መዘጋጀቷ ተገልጿል።