የሀገር ውስጥ ዜና

ከእንግዶች አቀባበል ጋር በተያያዘ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ዝግ የሚደረጉ መንገዶች…

By Yonas Getnet

February 11, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የተሽከርካሪ ፍሰቱን ለማሳለጥና ከእንግዶች አቀባበል ጋር በተያያዘ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን ይፋ አድርጓል፡፡

የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል 39ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ አስመልክቶ አጠቃላይ የጸጥታ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

የተሽከርካሪ ፍሰቱን ለማሳለጥና ከእንግዶች አቀባበል ጋር በተያያዘ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር ዝግ የሚደረጉ መንገዶችን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ መሰረትም ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ብራስ እንዲሁም ከቦሌ መድኃኒያለም በአትላስ ወደ ቅዱስ ኡራኤል ቤተ ክርስቲያን የሚወስደው መንገድ በመሪዎቹ ጉባዔ ምክንያት ከዛሬ የካቲት 4 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ለተሽከርካሪዎች ዝግ የሚደረግ ይሆናል።

በተጨማሪም በሌሎች እንግዶች በሚያርፉባቸው ዋና ዋና አደባባዮችና የአጀብ መስመሮች አሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠትና የትራፊክ ፖሊስ አባላትን ትዕዛዝ በማክበር የተለመደ ቀና ትብብራቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

በተጠቀሱት ቦታዎች ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪዎችን ማቆም የተከለከለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል፡፡

አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም ዜጎች በነጻ የስልክ መስመሮች 990፣ 991፣ 987፣ 816 እንዲሁም በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81ወይም በእጅ ስልኮች የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (Citizen Engagement Application) EFPApp በመጠቀም ጥቆማ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡