የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ይካሄዳል

By sosina alemayehu

February 11, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በዛሬው ዕለት ይካሄዳል፡፡

በ48ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ለመሳተፍም በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ስብሰባው “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የሚካሄደው።

የሚኒስትሮች የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በመደበኛ ስብሰባው ለ39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።

እንዲሁም ምክር ቤቱ በጥር ወር 2018 ዓ.ም 51ኛው የአፍሪካ ህብረት ቋሚ ተወካዮች ኮሚቴ በተወያየባቸው አጀንዳዎች ላይ ምክክር ያደርጋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ የአፍሪካ ሕብረት ተቋማትና አደረጃጀቶች፣ በምክር ቤቱ ስር የሚገኙ ኮሚቴዎችና ንዑሳን ኮሚቴዎች እንዲሁም የአጀንዳ 2063 የአፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያዳምጥም ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል አፍሪካ በፈረንጆቹ 2025 በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባዔ ላይ የነበራትን ተሳትፎ ይገመግማል።

በስብሰባው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞቿን በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ለመሳተፍ ዝግጅት ማድረጓ ተመላክቷል፡፡