አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአፍሪካ የጋራ ደህንነት፣ ነፃነት እና ብልጽግና አንድነት ወሳኝ ነው አሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።
48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።
ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በጉባዔው ለመሳተፍ ወደ አዲስ አበባ የመጡ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።
አፍሪካ በተለያዩ ዘርፎች ባለፈው ዓመት እድገቶች እና ተግዳሮቶች እንዳጋጠሟት አስታውሰው፤ የአፍሪካ ሀገራት በተለያዩ ቁልፍ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም መያዝ መቻላቸውን አንስተዋል።
ለአብነትም በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባዔ ላይ የአፍሪካን አንድነት አቋም አጉልቶ ማሳየት መቻሉን አውስተዋል።
የዓለም ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት ስጋት እየጨመረ መምጣቱን በማንሳት በተለይም አፍሪካ በቴክኖሎጂ፣ በማዕድናት እና በንግድ መስመሮች ላይ የፉክክር መስክ እየሆነች መሆኑን ተናግረዋል።
በቴክኖሎጂ፣ በወሳኝ ማዕድናት እና በንግድ መስመሮች ላይ እያደገ የመጣው የዓለም አቀፍ የጂኦፖሊቲካዊ ውጥረት በአፍሪካ ሰላም እና ደህንነት ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን አብራርተዋል።
አንዳንድ ዓለም አቀፍ ኃያላን አሁንም አፍሪካን የፉክክር መስክ አድርገው እንደሚመለከቱ ገልጸዋል።
የአህጉሪቱን ጥቅም ለመጠበቅ የአፍሪካ አንድነት እውነተኛ እና ጠንካራ መሆን እንዳለበት በመጥቀስ፤ አፍሪካ በበጎ አድራጎት ላይ ሳይሆን በእኩልነት እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ እውነተኛ አጋርነት ያስፈልጋታል ብለዋል።
በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ልማት ዙሪያ አጀንዳ 2063 እና አህጉራዊውን ነፃ የንግድ ቀጣና በመተግበር ረገድ ቀጣይነት ያለው እድገት ማሳየቷን ጠቅሰው፤ በሌሎች ዘርፎችም እንዲሁ መሻሻሎች መታየታቸውን አንስተዋል።
በአህጉሪቱ እነዚህን ስኬቶች ቢኖሩም አፍሪካ አሁንም የምታስበውን ለማሳካት ብዙ እንደሚቀር አንስተው አዲስ ቁርጠኝነት እና የጋራ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በዘላቂ ውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ላይ ትኩረት የሚያደርገው የዘንድሮ ጉባዔ የሁሉንም ሀገራት ፍላጎቶች ግምት ውስጥ በማስገባት በኡቡንቱ መርህ የሚመራ ትብብር እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፤ የህብረቱ ተቋማት በተለያዩ ዘርፎች ባከናወኗቸው ተግባራት የአህጉሩን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል ስራ መስራታቸውን ገልጸዋል።
በአብነትም የአፍሪካ ሕብረት የልማት ኤጀንሲ (አውዳ-ኔፓድ) እና የአፍሪካ በሽታ መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) የሰሩትን ስራ እና ያመጡትን ውጤት ጠቅሰዋል።
የተጀመሩ ተግባራት አጠናክሮ ለማስቀጠል የፋይናንስ ምንጭን ማጎልበት እንደሚገባ አስገንዝበው፤ አህጉራዊ የግል ተቋማትን ከመንግሥታት ጋር ማስተሳሰር ይገባል ነው ያሉት።
በዮናስ ጌትነት