ዓለምአቀፋዊ ዜና

ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበ ያለው የአፍሪካ ህብረት መዋቅራዊ ማሻሻያ አጀንዳ …

By sosina alemayehu

February 11, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ48ኛው የአፍሪካ ኅብረት የሥራ አስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባ ሊቀ መንበር የአንጎላ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ በአፍሪካ ህብረት መዋቅራዊ ማሻሻያ አጀንዳ ውስጥ ከፍተኛ እድገት ተመዝግቧል አሉ።

48ኛው የአፍሪካ ህብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሃሳብ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል።

አምባሳደር ቴቴ አንቶኒዮ በስብሰባው መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በህብረቱ መዋቅራዊ ማሻሻያ አጀንዳ የአመራር ምርጫ ሂደቶችን የማጠናቀቅ፣ የህብረቱን የአሰራር ስርዓት የማሻሻል ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።

“በአጀንዳ 2063” የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ እና ውጤታማነትን ለማሻሻል በህብረቱ ውስጥ የስራ ዘዴዎችን ማደስ ይገባልም ነው ያሉት።

በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ የአፍሪካን ድምጽ በዓለም ዓቀፍ መድረኮች በማጉላትና ስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማጠናከር ሀገራቸው አዎንታዊ አስተዋፅዖ ማበርከቷን አስረድተዋል።

ቡሩንዲ የሳህል ቀጣና የሰላምና ደህንነት አስተባባሪ እንድትሆን፣ በኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና በሩዋንዳ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት እንዲፈታ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።

እንዲሁም በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በሶማሊያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን እና በሊቢያ ለሚደረገው የሰላም ጥረት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

የአጀንዳ 2063 ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤ የህብረቱን ተቋማዊ ማዕቀፍና ስትራቴጂካዊ ሚና በማጉላት የፖሊሲ ወጥነትን ማረጋገጥ፣ አህጉራዊ አቋሞችን ማጣጣም እና ቁልፍ ውሳኔዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሀገራት በአህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እና የጋራ መግባባት በመድረስ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

የህብረቱ አባል ሀገራት ለመጪው ትውልድ ምኞት ምላሽ የሚሰጡ ተጨባጭ እና ውጤታማ ውሳኔዎችን እንዲያሳልፉ ጠይቀዋል።

በፈጣን ዓለም ዓቀፋዊ ለውጦች ውስጥ የአፍሪካን የጋራ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በሶስና አለማየሁ