የሀገር ውስጥ ዜና

ሰራዊቱ ለቀጣናው ደህንነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

By Yonas Getnet

February 11, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋት እና ደህንነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ልዩ ተወካይ እና የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ የድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ዋና አዛዥ አምባሳደር ኤል ሃጂ ኢብራሂማ ዲኔ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለቀጣናው ሰላም፣ መረጋጋትና ደህንነት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ኤል ሃጂ ኢብራሂማ ዲኔ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአውሶምን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋጽዖ አድንቀዋል።

በውይይቱ ሁለቱም ወገኖች በሶማሊያ እና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋትን ለማጠናከር በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን የአውሶም መረጃ አመልክቷል።

በዮናስ ጌትነት