የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን የምታቀርባቸው ተሞክሮዎች …

By Adimasu Aragawu

February 12, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ልታቀርባቸው የምትችላቸው በርካታ ተሞክሮዎች አላት አለ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት መግለጫ፤ ከየካቲት 6 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት ቀናት ሁለት ዐበይት ጉባዔዎችን ታስተናግዳለች ብለዋል።

39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና የአፍሪካ ጣሊያን ጉባዔን ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የ2063ቱን አጀንዳ ለማሳካት ዘላቂ የውሃ አቅርቦት ደሕንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ሥርዓቶችን ማረጋገጥ በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚካሄድ ጠቅሰው፤ ይህም አፍሪካ ለዘላቂ ልማት ያላትን ቁርጠኝነት ያንጸባርቃል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ልታቀርባቸው የምትችላቸው በርካታ ተሞክሮዎች እንዳላት ገልጸው÷ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ባለፉት 7 ዓመታት በሰራችው ስራ የደን ሽፋን ከ17 በመቶ ወደ 23 በመቶ ማሳደግ መቻሏን ጠቁመዋል።

በዚህም ለዘላቂ ልማት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳየት ችለናል ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የሃይድሮ፣ የነፋስና የፀሐይ ታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኢነርጂ ፍላጎትን ከማሳደግ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር ለመትረፍ መቻሉን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን በመከልከል ለታዳሽ ኃይል ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይታለች ብለዋል።

በከተማ የኮሪደር ልማትና የወንዝ ዳርቻ ልማት ከተሞችን ጽዱና ውብ ማድረግ፣ የአካባቢ ብክለትን የቀነሱ ደማቅ ከተሞችን የመፍጠር ጥረት በአዲስ አበባ በመጀመር በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች እየቀጠለች ትገኛለች ነው ያሉት።

ከፕላስቲክ የጸዳ አካባቢን ለመፍጠር የአንድ ጊዜ ፕላስቲክ መያዣዎችን በመከልከል ለዘላቂ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም አስመስክራለች ብለዋል።

በቀጣይነትም የውሃ ሀብቷን በአግባቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁለንተናዊ ርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በአድማሱ አራጋው