አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ (ኢባትሎ) በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 74 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘሁ አለ፡፡
ኢባትሎ የጥራት መስፈርቶችን በማሟላት የአይኤስኦ 9001:2015 ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት ማረጋገጫ እውቅና አግኝቷል፡፡
የእውቅና ሰርተፊኬቱን የኢባትሎ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) ከኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ (ኢ/ር) ተረክበዋል።
አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ፥ ዘመኑን የዋጀ እና በቴክኖሎጂ የታገዘ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እየተሰራ ነው።
ሰርተፊኬቱ በጭነት አስተላላፊነት፣ በወደብ ተርሚናል እና በሌሎች ዘርፎች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ይበልጥ ለማጠናከር አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
በተለይም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማጠናከር የዓለም አቀፍ ደረጃዎች ድርጅት ምዘና በሚያስቀምጣቸው መሥፈርቶች መሰረት ሥራዎችን ለማከናውን ያስችላል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይ በሁሉም ዘርፎች ዘመናዊ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አብዱልበር (ኢ/ር) አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በተለያዩ ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ÷ ለዚህም ተቋሙ ያዘመነው አሰራር ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት በተለያዩ ዘርፎች በተከናወኑ ሥራዎች 74 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ጠቁመው ፥ አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ59 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ተስማሚነት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር መዓዛ አበራ (ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ የአገልግሎት እና ምርት ጥራትን ይበልጥ ለማጠናከር ከሚመለከታቻው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በኢባትሎ የተዘረጋው የአሠራር ሥርዓት የዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርትን የሚያሟላ እና የደንበኞችን እርካታ የሚያሳድግ እንደሆነ በኦዲት በመረጋገጡ የአይኤስኦ እውቅና መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡
ሁሉም የግልና የመንግሥት ተቋማት የጥራትን ጽንሰ ሀሳብ በሚገባ በመረዳት ምርትና አገልግሎታቸው የደንበኞችን እርካታ የሚያረጋግጥ እንዲሆን መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ