አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) እንደ ሀገር ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ በተቀመጡ አቅጣጫዎች የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል አሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፡፡
የብልጽግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎች ድጋፋዊ ሱፐርቪዥን የግምገማ መድረክ ተጠናቅቋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በየደረጃው የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት በተደረጉ ጥረቶች የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል።
በፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለማሳካት አመራሩ ከህዝቡ ጋር በመተባበር በቁርጠኝነት ርብርብ ማድረጉን አንስተዋል፡፡
በዚህም የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት፣ በኮሪደር ልማት፣ ሰላም በማጽናት፣ በዲጂታላይዜሽን፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በመሰረተ ልማትና ሌሎች ዘርፎች የተቀመጡ ግቦችን በማሳካት ረገድ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡንና መልካም ልምዶች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ተሞክሮዎችን በማስፋትና ለእያንዳንዱ ግብ ባለቤት በመፍጠር እንዲሁም ተቋማትን በማቀናጀትና ቀጣይነት ያለውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ለበለጠ አፈጻጸም መትጋት ይገባል ነው ያሉት፡፡
የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮችና መሻሻል በሚገባቸው አፈጻጸሞች ዙሪያ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።