የሀገር ውስጥ ዜና

የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ተሳታፊዎች የዓድዋ ድል መታሰቢያን እንዲጎበኙ …

By sosina alemayehu

February 12, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ የሚመጡ እንግዶች ለአፍሪካውያን ትልቅ የፓን አፍሪካኒዝም ምልክት የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያን እንዲጎበኙ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) ለፋና ዲጅታል እንዳሉት፤ የዓድዋ ድል የመላው የጥቁር ሕዝቦች ድል ነው።

ከዓድዋ ድል 128 ዓመታት በኋላ እውን የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ የገነባበት መንገድ ታሪክን እንዲያሳይ ተደርጎ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የበርካታ የሀገራት መሪዎች የዓድዋ ድል መታሰቢያን መጎብኘታቸውን አስታውሰው፤ መሪዎቹ የዓድዋ ድልን በሀገሮቻቸው እንዲተዋወቅ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

መሪዎችን ጨምሮ በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ለመሳተፍ የመጡ እንግዶች የዓድዋ ድል መታሰቢያን እንዲጎበኙ ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የዓድዋ ድል የጥቁሮች የነጻነት ጮራ ታሪክ መሆኑን የማስገንዘብ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

መታሰቢያውን ሙሉ በሙሉ ጎብኝቶ መጨረስ ረዥም ጊዜ የሚወስድ እንደሆነ ገልጸው፤ እንግዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጎበኙ የሚያስችል መርሐ ግብር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛ እና ፖርቹጊዝን ጨምሮ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ አስጎብኚዎች ዝግጁ  መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በዮናስ ጌትነት