አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማረጋገጥ ከፖሊሲ ማዕቀፍ ባሻገር የአኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን ትግበራ ማፋጠን ይገባል አለ የአፍሪካ ኅብረት።
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ በተደረገባቸው አምስት ሀገራት የተገኙ ውጤቶችን በመገመገም ወደ ሌሎች ሀገራት ለማስፋት ያለመ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኅብረቱ የኢኮኖሚ ልማት፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኮሚሽነር ፍራንቺስካ ቤሎቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በአፍሪካ ንግድና ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት አዳዲስ መርሐ ግብሮችን ከማስተዋወቅ ይልቅ ትግበራ ላይ ማተኮር ይገባል።
የአጀንዳ 2063 ግብ እንዲሳካና በተለይም የኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማረጋገጥ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ተግባራዊ በተደረገባቸው ሀገራት የተገኘውን ውጤት በመላ አኅጉሪቱ ማስፋፋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በአፍሪካ ኅብረት የጃፓን አምባሳደር ኔቦሩ ሴክጉቺ በበኩላቸው፥ ሀገራቸው በጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) አማካኝነት ለነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራ ውጤታማነት በትብብር ስትሰራ መቆየቷን አንስተዋል።
የኢንዱስትሪ ሽግግርና የንግድ ትስስር ሊነጣጠል እንደማይችል ገልጸው÷ ጃፓን ለአፍሪካ የኢንዱስትሪ እድገትና ቀጣናዊ ንግድን ለማስፋፋት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በአኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናው አማካኝነት የተፈጠረውን የገበያ እድል ለዘላቂ ልማት ለመጠቀም በአፍሪካ ያለውን እምቅ የመልማት አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የነጻ ንግድ ቀጣናው በኬንያ፣ ጋና፣ ግብጽ፣ ናሚቢያ እና ሲሼልስ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፥ የትግበራ ሂደቱ ችግሮችን በመለየት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማጠናከር መንገድ ያመላከተ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ዋና ጸሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ፥ በአምስቱ ሀገራት የተገኘው ውጤት የኢንዱስትሪ ፖሊሲን ከንግድ ጋር ለማስተሳሰር ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ አመልክተዋል።
የንግድ ትስስርን የማጠናከር ስራ ከኢንዱስትሪ ልማት ጋር ተሰናስሎ መተግበር እንዳለበት ጠቅሰው፥ በትግበራ ሂደቱ የተገኘው ልምድ የእሴት ሰንሰለቱን ቀልጣፋ ለማድረግና አካታች እድገትን ለማረጋገጥ ያግዛልም ነው ያሉት።
በኃይለማሪያም ተገኝ