አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል አሉ የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት መሪዎች።
በ39ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ ትናንት አዲስ አበባ የገቡት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር ተወያይተዋል።
ዋና ፀሐፊው በውይይቱ ወቅት፤ የአፍሪካ ህብረትን ድምጽ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ በማሳደግ ረገድ እየተሰራ ያለውን ስራ አድንቀዋል።
አፍሪካ በባለብዙ ወገን ማሻሻያዎች ላይ ገንቢ ሚና እንዳላት ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት እና የአፍሪካ ህብረት ዘርፈ ብዙ ስትራተጂካዊ ትብብር እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ዋና ጸሐፊው የአፍሪካ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነትን እንዲጠናከር ላሳዩት ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት አጋርነት ሰላምን፣ ደህንነትን እና ዘላቂ ልማትን ለማፋጠን ወሳኝ መሳሪያ መሆኑንም አንስተዋል።
ሁለቱ መሪዎች ከአጀንዳ 2063 እና ከተባበሩት መንግስታት ቻርተር ጋር የተጣጣመ ትብብርን ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
መሪዎቹ በቀጣናዊ ሰላም እና ደህንነት፣ ዘላቂ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሽግግር፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት ዙሪያ መክረዋል።
የአፍሪካ የልማት ፋይናንስ ፍላጎቶች በበቂ ሁኔታ እንዲፈቱ ፍትሐዊ የፋይናንስ ተደራሽነት፣ የተረጋጋ የዕዳ ሥርዓት እና የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቶች እንዲሻሻሉ ለማስቻል መስራት እንደሚያስፈልግ ተግባብተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ማሻሻያ በማድረግ አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ ውክልና ሊኖራት እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በዮናስ ጌትነት