አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ የስራ ዘመን 5ኛ ዓመት 10ኛ መደበኛ ጉባኤ በነገው ዕለት በአዳማ ጨፌ አዳራሽ መካሄድ ይጀምራል።
የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ ሰዓዳ አብዱራህማን ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ጨፌው በአባላቱ እና ቋሚ ኮሚቴዎች የተደረጉ የአፈጻጸም ክትትል ሪፖርቶች ቀርበው ውይይት ያደርጋል ብለዋል።
የጨፌ አባላትና ቋሚ ኮሚቴዎች የክትትል እና ቁጥጥር እንዲሁም የመስክ ምልከታ በማድርግ የክልሉን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ስራዎች መመልከታቸውን ገልጸዋል።
የክትትል እና ቁጥጥር እንዲሁም የመስክ ምልከታ ግኝቶች ሪፖርት ውይይት እንደሚደረግበትም ጠቁመዋል።
በክልሉ ያለፉት 6 ወራት የመንግስት የስራ አፈጻጸም ዕቅድ ክንውን ላይ ውይይት ይደረጋል ያሉት አፈ ጉባኤዋ፤ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎች የተገኙ ውጤቶች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ጉባኤው የዳኞች ሹመትን ጨምሮ የተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ በመወያየት ያፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው ያመለከቱት።