የሀገር ውስጥ ዜና

የናይል ትብብር ማዕቀፍ አባል ሀገራት በናይል ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ላይ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ

By Melaku Gedif

February 13, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን ያጸደቁ ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲ እና ደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል፡፡

ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሙሉ በመሉ በሚተገበርበትና እና የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን በፍጥነት መቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

የናይል ትብብር ማዕቀፍ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች በዚህ ወቅት በናይል ወንዝ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርሕ ላይ ቁርጠኛ አቋም ያላቸው መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ስምምነቱ አባል ሀገራቱ በወንዙ ያላቸውን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበርክትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡