ዓለምአቀፋዊ ዜና

የተባበሩት መንግስታት ለአፍሪካ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል – አንቶኒዮ ጉተሬዝ

By Hailemaryam Tegegn

February 14, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የተባበሩት መንግስታት ለአፍሪካ ልማትና ብልጽግና የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል አሉ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፡፡

39ኛው የኅብረቱ የመሪዎች ጉባዔ “ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደህንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፥ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ መካሄድ ጀምሯል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንደሚያስፈልጋት አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኅብረቱ በሰላም፣ በዘላቂ ዕድገት ግብና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚደነቁ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ያሉት ዋና ጸሃፊው፥ በደቡብ ሱዳን እንዲሁም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የነበረውን ግጭት ለመፍታትና ለማረጋጋት በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ዕድገት አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከርና ሰላም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸው፥ ኅብረቱ በፍትሃዊነትና በእኩልነት ላይ የሚሰራው ስራ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ወቅቱ የፖለቲካ ሽግግር በስፋት ያለበት መሆኑን ጠቁመው፥ ዓለም አቀፍ አጋርነት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

አፍሪካ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተወዳዳሪ መሆን እንድትችል ሁሉም የአህጉሪቱ ሀገራት የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ