አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ (ኢ/ር) የተመራ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑክ ላለፉት ሶስት ቀናት በጀርመን ሙኒክ በተካሄደው 62ኛው የሙኒክ የፀጥታ ኮንፈረንስ ላይ ተሳትፏል።
ኮንፈረንሱ በሕግ ላይ በተመሰረተው ዓለም አቀፍ ሥርዓት ላይ የተደቀኑ ተግዳሮቶችን በመፈተሽ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው።
በመድረኩ እንደ የፀጥታ ስጋቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የንግድ ጦርነት፣ ፍልሰትና በምግብ ዋስትና ሥርዓቶች ውስጥ ያሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት በዓለም አቀፍ ተዋናዮች መካከል ከመከፋፈል ይልቅ በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል።
ከመድረኩ ጎን ለጎን ሚኒስትሯ ከጀርመን የመከላከያ ሚኒስትር ቦሪስ ፒስቶሪየስ ጋር ውጤታማ የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱም በሀገራቱ መካከል ያለውን ወታደራዊና የመከላከያ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከርና ለጋራ ጥቅም በቅርበት ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
በተጨማሪም ሚኒስትሮቹ በጋራ በመስራት ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ወታደራዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ በሁለቱ ሀገራት መካከል ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በፈረንጆቹ 1963 የተመሰረተው የሙኒክ የፀጥታ ኮንፈረንስ በዓለም አቀፍ የደህንነት ፖሊሲዎች ላይ የሚመክር መድረክ ነው።
በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሀገር መሪዎችን፣ ሚኒስትሮችን፣ የጦር አዛዦችን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት መሪዎችንና የዘርፉን ምሁራን ተሳትፎ ያደርጋሉ።
መድረኩ ዓለም አቀፍ ግጭቶችን በውይይት ለመፍታትና በፀጥታ ዙሪያ ትብብርን ለማጠናከር እንደ ትልቅ የዲፕሎማሲ መድረክ የሚያገለግል መሆኑን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።
በመላኩ ገድፍ