ቢዝነስ

ኢትዮጵያ ከቁልፍ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላትን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ታጠናክራለች – አቶ አህመድ ሺዴ

By Yonas Getnet

February 15, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከቁልፍ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላትን አጋርነት ታጠናክራለች አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በተደረጉ ስብሰባዎች ቁልፍ ከሆኑ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር የሚያጠናክር ተግባር አከናውኗል።

አቶ አህመድ ሺዴ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) እና ከአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት (BADEA) መሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይቶቹ የኢትዮጵያን የሪፎርም አጀንዳን፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ኢንቨስትመንቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም የሚደረጉ ጥረቶችን መደገፍ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት አድርገው መክረዋል።

የአረብ ባንክ ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ልማት ፕሬዚዳንት አብዱላህ አልሙሳይቤህ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ጨምሮ ለዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን የፋይናንስ ዕድልን መፍጠር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

እንዲሁም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ኬቨን ካሪዩኪ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ባንኩ የኢትዮጵያ የኢነርጂ ልማትን ለማስፋት፣ ቀጣናዊ ውህደትን ለማጠናከር እና ቁልፍ ፕሮጀክቶችን ለማፋጠን ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጧል።

ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄራርዲን ሙኬሺማና ጋር ባደረጉት ልዩ ስብሰባ ሁለቱም ወገኖች የግብርና ልማትን ለማስፋፋት እና የአየር ንብረት ለውጥ ጫናን ለመቋቋም እየተተገበሩ የሚገኙ መርሐ ግብሮች ከኢትዮጵያ አጀንዳዎች ጋር የተጣጣሙ ማድረግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

በተደረጉት ስብሰባዎች የፋይናንስ ተቋማቱ ዘላቂ እና ሁሉን አቀፍ ልማት ለማምጣት የጋራ ቁርጠኝነት ማሳየታቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል።