አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በኦሮሚያ ክልል አስተናጋጅነት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆየው ሀገር አቀፍ የአዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና እና ምዘና ውድድር በስኬት ተጠናቅቋል።
“የአዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለኢትዮጵያ ከፍታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከየካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የተካሄደው ውድድር የሀገርን ገጽታ ለመገንባት እና አንድነትን ለማጠናከር ስፖርት የላቀ ፋይዳ እንዳለው ያሳየ መሆኑ ተገልጿል።
ከ13 እስከ 15 ዓመት በታች የአዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ምዘና ውድድር አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች በትክክለኛ የዕድሜ ተሳትፎ ከ1 እስከ 3 በመሆን በአሸናፊነት አጠናቅቀዋል።
በምዘና ውድድሩ በኦሎምፒክ ስፖርቶች አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ክልል እንዲሁም አዲስ አበባ ከ1ኛ እስከ 3ኛ ያለውን ደረጃ ሲይዙ፤ በፓራሊምፒክ ስፖርት ደግሞ ኦሮሚያ ክልል፣ አዲስ አበባ እና አማራ ክልል ከ1ኛ እስከ 3ኛ በመያዝ አጠናቅቀዋል።
ለኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እና ለተለያዩ ስፖርት አካዳሚዎች አዳጊ ስፖርተኞችን በማስመረጥ ረገድ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 26 በማስመልመል ቀዳሚ ሆነዋል።
ጋምቤላ ክልል 24 አዳጊዎችን በማስመረጥ 3ኛ ደረጃን ይዟል።
በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድበውድድሩ ማጠቃለያ መርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በስፖርት ተወዳዳሪና አሸናፊ ሀገር ለመፍጠር የአዳጊ ስፖርተኞች ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራችን በሌሎች ዘርፎች እያስመዘገበች ያለዉን ውጤት በስፖርቱ ለመድገም እየተሠራ ነው ብለዋል።
የምዘና ውድድሩ በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ማጎልበቱን እና የአዘጋጇን ከተማ ኢኮኖሚ ማነቃቃቱን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ውድድሩ በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁሉም ባለድርሻዎች ሚና ከፍተኛ እንደነበር ገልጾ፤ ለነበራቸው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርቧል።