የሀገር ውስጥ ዜና

ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የሚገነባው የድሬዳዋ ፕሮጀክት…

By Adimasu Aragawu

February 16, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከ1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የድሬዳዋ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ተጀምሯል፡፡

ግንባታውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር አስጀምረዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ የፍሳሽ ማስወገጃና ማጣሪያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክት ለማህበረሰቡ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ ለአካባቢው ዜጎች ከፍተኛ የስራ እድል ይፈጥራል፡፡

የአስተዳደሩን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን የውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው÷ ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የግንባታ ሂደቱ ተሳታፊዎች በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ፕሮጀክቱ በመቐሌ፣ አዳማ፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሳና በባሕር ዳር የሚተገበር መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

አቶ ከድር ጁሀር በበኩላቸው÷ ድሬዳዋ የነጻ ንግድ ቀጣና በመሆኗ የዕድገት ግስጋሴዋን የሚመጥን የውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ያስፈልጋታል ነው ያሉት፡፡

የግንባታ ፕሮጀክቱ የአስተዳደሩን የፍሳሽ አያያዝና አወጋገድ ስርዓትን በላቀ ደረጃ የሚያሻሽል እንደሆነ መናገራቸውን የከተማ አስተዳደሩ ኮሙኒኬሽን ለፋና ዲጂታል ገልጿል።

ለግንባታ ፕሮጀክቱ ከተማ አስተዳደሩ 13 ሄክታር የግንባታ መሬት የማዘጋጀት፣ ከአካባቢው ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች ከ28 ሚሊየን ብር በላይ የካሳ ክፍያና የምትክ መሬት ቦታን በማዘጋጀት ለስኬታማነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እና እገዛ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡