የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ታሪካዊ ግንኙነት…

By Melaku Gedif

February 16, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እና ቱርክዬ ታሪካዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት 16ኛው ክፍለ ዘመን የኦቶማን ኢምፓየር የቀይ ባሕር ወደቦችን ሲቆጣጠር የተጀመረ ሲሆን ÷ ግንኙነቱ በሒደት ወደ ዘላቂ እና ተግባራዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አድጓል።

በፈረንጆቹ 1896 ሱልጣን አብዱልሀሚድ 2ኛ እና ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ይፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በመጀመራቸው ቱርክዬ በ1912 በሐረር ቆንስላ ጽ/ቤት መክፈት ችላለች፡፡

ቱርክዬ በፈረንጆቹ 1926 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተች ሲሆን ÷ ኢትዮጵያ ደግሞ በ1933 ኤምባሲዋን በአንካራ ከፍታለች፡፡

የ19ኛው ክፍለ ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ልውውጦች ቱርክዬ በአዲስ አበባ ኤምባሲ እንድትከፍት፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ አጋርነት እንዲገነባ፣ ኢንቨስትመንት እና መሠረተ ልማት እንዲስፋፋ፣ ንግድ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዲያድግ አድርጓል፡፡

ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ቱርክዬ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አድርጋለች፡፡

በቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መልካም የነበረ ሲሆን ÷ ንጉሠ ነገሥቱ በ1967 እና በ1971 ሁለት ጊዜ ቱርክዬን ጎብኝተዋል፡፡

በደርግ ዘመነ መንግሥት በአንካራ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በተዘጋበት ወቅት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የሻከረ ሲሆን ÷ በፈረንጆቹ 2006 ግንኙነቱ እንደገና ቀጥሏል፡፡

የቱርክዬ እና ኢትዮጵያ ዘመናዊ ስትራቴጂካዊ ትስስር እና ግንኙነት እያደገ የመጣ ሲሆን ÷ ቱርክዬ በቀጣናው መረጋጋት እና ኢኮኖሚ ልማት ላይ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ትገኛለች፡፡

የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በፈረንጆቹ 2015 በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን÷ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በ2017 በቱርክዬ ባደረጉት ጉብኝት ከፕሬዚዳንቱ ጋር ተገናኝተዋል።

የቱርክዬ መንግሥት ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች የቅድመ ምረቃ እና የድህረ ምረቃ ነጻ የትምህርት ዕድል ይሰጣል። በዚሁም በፈረንጆቹ 2020፤ 632 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በተለያዩ የቱርክዬ ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት ዕድል አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በአንካራ ተገናኝተው ወታደራዊ ስምምነቶች መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

በ16ኛው ክፍለ ዘመን የጀመረው የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት አሁንም ድረስ በተለያዩ ዘርፎች ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

👉ለፈጣን እና ወቅታዊ መረጃዎች የፋና ዲጂታል አድራሻዎችን ከአስተያየት መስጫ ሳጥን ያግኙ፡-