ጤና

በወሊድ ወቅት ጽኑ ሕመም ላይ ለነበረች እናት ደም በመለገስ ሕይወቷን የታደገው ዶክተር..

By Yonas Getnet

February 16, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በወሊድ ወቅት ጽኑ ሕመም ላይ ለነበረች እናት ከስጦታወች ሁሉ የላቀውን ደም በመለገስ ሕይወቷን መታደግ የቻለው ዶክተር በበርካቶች ዘንድ ምስጋና ተችሮታል፡፡

ዶክተር ሰይድ አሕመድ ይባላል፡፡ በከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ነው፡፡

አንዲት የ32 ዓመት እናት ለወሊድ አገልግሎት ወደ ከሚሴ ጠቅላላ ሆስፒታል ትሄዳለች፡፡

ይሁን እንጂ ወደ ሆስፒታሉ የደረሰችው ምጥ ከጀመራት ዘግይታ በመሆኑና ብዙ ደም ስለፈሰሳት አስቸኳይ ቀዶ ሕክምና እንዲሰራላት ወደ ዶክተር ሰይድ ክፍል አመራች፡፡

እናት ብዙ ደም ስለፈሰሳት ለቀዶ ሕክምና ሥራው ደም ያስፈልግ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በሆስፒታሉ ምንም አይነት የደም አቅርቦት አልነበረም፡፡ ይህም ቀዶ ሕክምናውን ለማከናወን ከባድ ፈተና እንደሆነበት ዶ/ር ሰይድ ይናገራል፡፡

ለሕክምናው 4 ዩኒት ደም ያስፈልግ ነበር ያለው ዶክተር ሰይድ÷ የእርሱ የደም አይነት ከወላዷ እናት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑና ሌሎች የጤና ባለሙያዎችን ግንባር ቀደም ሆኖ በማስተባበር ደሙን በመለገስ ቀዶ ሕክምናውን በስኬት ማከናወን ችሏል፡፡

ወላዷ እናት በሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ክትትልና ርብርብ ልጇን በሰላም ተገላግላ ወደ ቤቷ የተመለሰች ሲሆን ÷ አሁን ላይም በሙሉ ጤንነት ላይ ትገኛለች፡፡

የእናቶችን ሞት መታደግ ዋነኛ አላማችን ነው የሚለው ዶክተር ሰይድ÷ አርአያ ሆኖ ደሙን በመለገስ የአንዲትን እናት ሕይወት መታደግ በመቻሉ መደሰቱን ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተናግሯል፡፡