የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አርዓያነት ያለው አስተዳደር ለቀጣናው ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል – ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን

By Hailemaryam Tegegn

February 17, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ባላት የረዥም ዘመናት የመንግስት ስርዓትና አርዓያነት ያለው አስተዳደር በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያላት ሚና እያደገ ነው አሉ የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በዚሁ ወቅት፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ያስገኟቸውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች አድንቀው፥ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ያላት ትብብር ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፥ የሁለቱን ሀገራት የረዥም ዘመናት ግንኙነት ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የዓለም ዓይኖች ወደ አፍሪካ ቀንድ ቀጣና እያማተሩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት የመንግስት ስርዓትና አርዓያነት ያለው አስተዳደር በቀጣናው ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዛሬው ጉብኝት ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት እምነታቸውን ገልጸው፥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ ህዝብ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል አመስግነዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመግለጫቸው በነገው ዕለት የሚጀመረውን የረመዳን ጾም በማስመልከት ለኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡