የሀገር ውስጥ ዜና

ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ተከልክላ መቆየቷ ትክክል አይደለም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Hailemaryam Tegegn

February 17, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ተከልክላ መቆየቷ ትክክል አይደለም አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት እያደረጉ ከሚገኙት የቱርክዬ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን ጋር የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ ዓመት የ10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት እንደምትጠብቅ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

ከ130 ሚሊየን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ የባህር በር ተከልክላ በዓለም ላይ ካለው ልምምድ ውጪ በጠላቶቻችን ደባ ለረዥም ጊዜ የጆኦግራፊ እስረኛ ሆና እንድትቆይ መደረጉ ትክክል አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ፈጣን የእድገት ጉዞ ለማስቀጠል ቱርክዬ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ማግኘት የምትችልበትን ሁኔታ እንዲያግዙ በስፋት ተወያይተናል ነው ያሉት፡፡

በተለይም ሎጅስቲክስ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፥ ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይፕ ኤርዶዋን በዚህ ሂደት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ መክረናል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ሁለቱ ሀገራት በጸረ ሽብር ትግል በጋራ ለመስራት መስማማታቸውንም አንስተዋል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ