የሀገር ውስጥ ዜና

በቄለም ወለጋ ዞን የተመለከትነው ሥራ ኃብትን በአግባቡ በመጠቀም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Melaku Gedif

February 18, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በቄለም ወለጋ ዞን የተመለከትነው ሥራ ኃብትን በአግባቡ በመጠቀም ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ÷ ዛሬ በቄለም ወለጋ ዞን ሃዋ ገላን ወረዳ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የለማ የሙዝ እርሻ ከባቢን ጎብኝቻለሁ ብለዋል፡፡

‎በጉብኝታቸውም አርሶ አደሮች በፍጹም ጽናት፣ ቅንጅት እና ትብብር አካባቢያቸውን በቀየረ ሥራ በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

የተመለከትነው የእርሻ ሥራ የአካባቢ መሬትን እና የውኃ ኃብትን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ባህላዊ የመስኖ ዘዴዎችን በመጠቀም እና በቅርብ ያለ ኃብትን በሚገባ ጥቅም ላይ በማዋል ማኅበረሰቡ ውጤታማ እና ተስፋ ሰጪ የግብርና ማዕከል መፍጠር ችሏል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ።

በተለይም የመንገድ መሠረተ ልማት የአርሶ አደሮችን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ለማድረስ የፈጠረውን እድል መመልከት እጅግ የሚያበረታታ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

ይህ እድገት የልማት ጥረቶች ከአካባቢው ማኅበረሰብ ፍላጎት እና አቅም ጋር በቅርበት ሲናበቡ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት በግልጽ የሚያሳይ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።