አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአርጆ ዲዴሳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ለአገልግሎት ሲበቃ የምግብ ሉዓላዊነት ጥረቶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችን በመጥቀም ግብርናውን የሚያሻግር ይሆናል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ የአርጆ ዲዴሳ የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን የጎበኘሁ ሲሆን የደረሰበት ደረጃም አስደናቂ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል።
ይኽ ትልቅ ፕሮጀክት በቅርብ ዓመታት ግንባታው ተፋጥኖ ወደ መጠናቀቂያው ተቃርቧልም ነው ያሉት።
ለአገልግሎት በሚበቃበት ጊዜም የተለያዩ የአዝርዕት ልማትን በመደገፍ እንደሀገር የጀመርነውን የምግብ ሉዓላዊነት ጥረቶች እና በሺዎች የሚቆጠሩ አርሶአደሮችን በመጥቀም ግብርናውን የሚያሻግር ይሆናል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ባላሰለሰ ጥረት እና የታቀደለትን ግብ በማሳካት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ኑሮ ከፍ እንደሚያደርግ እተማመናለሁ ሲሉም አመልክተዋል።