አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ የጸጥታና ደኅንነት ሥራ የተመራበት መንገድ በምሳሌነት የሚወሰድ ነው አሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔና 2ኛው የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ እንዲሁም የቱርክዬ ፕሬዚዳንት በአዲስ አበባ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ የጸጥታ ዕቅድ አፈጻጸሙን ገምግሟል።
ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ 39ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እና በ2ኛው የጣሊያን አፍሪካ ጉባዔ ላይ ከ20 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።
በዚህም የጸጥታ መዋቅሩ የተልዕኮ ስፋት፣ የእጀባ እና ጥበቃ ሥርዓት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን ገልጸው ÷ የአዲስ አበባን ልማትና ዕድገት አጉልቶ በማሳየት ሀገራችንን ያስተዋወቀ ነው ብለዋል።
በእጀባና በጥበቃ ሥራው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጸጥታ ኃይል ስምሪት ወስዶ ሰፊ ቦታ የሸፈነበት፣ በበቂ የሎጂስቲክ አቅርቦት የታገዘና የቴክኖሎጂ ስምሪቱም በዚያው ልክ ያደገበት እንደነበርም አመልክተዋል።
ያለፈውን ልምድ መነሻ በማድረግ የተቀናጀ ሥርዓት በመፈጠሩ የጸጥታና ደኅንነት ሥራ መሳካቱን የጠቀሱት ኮሚሽነር ጀነራሉ÷ ጉባዔው በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን ያበረከቱ አካላትን አመስግነዋል።