የሀገር ውስጥ ዜና

የሶርጋ ኢኮ ሎጅ ፕሮጀክት ግንባታ በቅርቡ ይጠናቀቃል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

February 19, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሶርጋ ኢኮ ሎጅ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራ በቅርቡ ይጠናቀቃል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ በሶርጋ ሐይቅ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን ሶርጋ ኢኮ ሎጅ መጎብኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

በሶርጋ ሐይቅ ላይ የሚገኘው የሶርጋ ኢኮ ሎጅ በአሁኑ ወቅት በ14 ሄክታር መሬት ላይ እየተገነባ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ሥራ በፍጥነት እየተከናወነ ሲሆን÷በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ‎ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ከነቀምቴ ከተማ በ6 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ብቻ የሚገኘው የሶርጋ ኢኮ ሎጅ አካባቢውን ከመጠበቅ ባሻገር በኮንስትራክሽንና በተለያዩ አገልግሎቶች የሥራ እድል እንዲፈጥር ተደርጎ የተቀረፀ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ማሕበረሰብ በመጥቀም በክልሉ ዘላቂ ቱሪዝምን የሚያበረታታ እንደሚሆን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሱት።