የሀገር ውስጥ ዜና

በወለጋ አካባቢ ያየናቸው የልማት ስራዎች ሀገራችንን ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች ማሳያ ናቸው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Adimasu Aragawu

February 19, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በወለጋ አካባቢ ያየናቸው የልማት ስራዎች ሀገራችንን ለመቀየር የሚያስችሉ ስራዎች ማሳያ ናቸው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ የወለጋ ዞኖች ያደረጓቸውን የልማት ሥራዎች ጉብኝት አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ነው።

በዚህም ሀገሪቱን ለመለወጥ ከተያዙ አምስት ዋና ዋና ዘርፎች መካከል በግብርና፣ ማዕድን፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም ዘርፎች የተሰሩ ስራዎችን በጉብኝቱ ወቅት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

የወለጋ አካባቢ ዞኖች ከለውጡ በፊትና በኋላ በአለመረጋጋት እንደሚታወሱ ጠቅሰው÷ አሁን ላይ ግን በአካባቢው ሕብረተሰቡ ሰላማዊ እንደሆነና አርሶ አደሮች፣ ሴቶች እንዲሁም ወጣቶች ወደ ሥራ መግባታቸውን አመልክተዋል።

እየተገነቡ ያሉ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢውን ጸጋ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው÷ እነዚህ ሁሉ ሲተሳሰሩ የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት ማምረት ብቻ ሳይሆን ያመረትናቸውን ማቀነባበር የሚችል የአግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች ስላልነበሩ ብዙ ጊዜ በጥሬና አንዳንዴም ተበላሽተው የመቅረት አጋጣሚዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

አሁን ግን ዓመቱን ሙሉ ማምረት የሚቻልበትና ከአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች ጋር ለማስተሳሰር ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቁመዋል።

ነቄምቴ ከተማ በኮሪደር ልማት መቀየሯንና ሕብረተሰቡም በዚህ ደስተኛ መሆኑን በጉብኝታቸው ወቅት መመልከታቸውን ጠቅሰው÷ ለተደረገላቸው አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል።

በአድማሱ አራጋው