አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በህገ ወጥ መንገድ ነዳጅ ሲቀዱ የተያዙ ሁለት የነዳጅ ማደያ ሰራተኞች በእስራት እና በገንዘብ ተቀጡ።
የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው ተከሳሾች አዲስ ሙሉጌታ እና ሀረገወይን ዳጉ የተባሉ የኦላ ነዳጅ ማደያ ሰራተኞች ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል የሞጆ ከተማ ዓቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ተከሳሾቹ ላይ የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ስርዓት ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1363/2017 አንቀጽ 25 ስር የተደነገገውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ ክስ አቅርቦባቸዋል።
በክሱ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ተከሳሾቹ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ላይ በህግ ከተፈቀደ አሰራር ውጪ ያለ አግባብ 4 ሺህ ሊትር ነዳጅ በጄሪካን ሲቀዱ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ተከሳሾቹ በሞጆ ከተማ ሎሜ ወረዳ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ እንዲከላከሉ በሰጠው ብይን ተከሳሾቹ ማስረጃውን በተገቢው ማስተባበል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል።
ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት መርምሮ 1ኛ ተከሳሽ በ3 ዓመት ከ3 ወር ጽኑ እስራት እንዲሁም 2ኛ ተከሳሽ በ3 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
በተጨማሪም ተከሳሾቹን እያንዳንዳቸው 350 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን፤ የተያዘው ነዳጅ ተሽጦ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ