የሀገር ውስጥ ዜና

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዲስ መለዮ ይፋ አደረገ

By Hailemaryam Tegegn

February 20, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በተገኙበት አዲስ መለዮ ይፋ አድርጓል፡፡

የዕዙ 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በተለያዩ ስነስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

በስነስርዓቱ ላይ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ከቀይ ቦኔት መለያው በተጨማሪ በክንድ ላይ የሚጠቀመው አዲስ መለያ ይፋ ተደርጓል።

የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አዲሱ መለዮ የዕዙን የጋራ ዓላማና የመንፈስ ጥንካሬ የሚያሳይ ነው፡፡

በተጨማሪም የዕዙን የልብ ትርታና ዝግጁነት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸው፥ የታሪክ ማህደር ከመሆን ባለፈ ለዕዙ የግዳጅ መነሳሻ ሆኖ ያገልግላል ነው ያሉት፡፡

በሌላ በኩል የዕዙን የድል ዓመታት ጉዞ የሚተርክ መጽሃፍ ምረቃ መርሐ ግብር ተካሂዷል።

የዕዙ የምስረታ በዓል ለሚቀጥሉት ሦስት ቀናት በተለያዩ ስነስርዓቶች የሚቀጥል ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም የዕዙን ምስረታ ምክንያት በማድረግ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ መካሄዱ የሚታወስ ነው፡፡

በመራኦል ከድር