አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሰራ ነው አለ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ (ኢባትሎ)፡፡
የኢባትሎ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል እንዳሉት ÷ ኢትዮጵያን ከዓለም ገበያ ጋር በማስተሳሰር የገቢ እና ወጪ ንግድን ለማሳለጥ እየተሰራ ነው፡፡
ዘንድሮ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 40 ከመቶ በላይ እቃዎች በኢባትሎ መጓጓዛቸውን ጠቁመው ÷ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትኩረት መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ይህም ደንበኞች በያሉበት ሆነው ዋጋ ለመነጋገር እንዲሁም የተጫኑ እቃዎች ከመነሻ ጀምሮ እስከ መዳረሻ የሚያልፉበትን ሒደት ለመከታተል ያስችላቸዋል ነው ያሉት፡፡
በቅረቡ ይፋ የሚደረገው ይህ ሥርዓት ግልጽ፣ ተዓማኒ፣ ቀልጣፋ፣ ተመጣጣኝ እና ተወዳዳሪ ዋጋ ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ አመልክተዋል፡፡
በቀጣይ ኢባትሎ ተወዳዳሪነቱን ለማጠናከር በቅንጅት ይሰራል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ እቅዱን ለማሳካትም ያሉትን መርከቦች ቁጥር ማሳደግ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
በቀጣይ አምስት ዓመታት ተጨማሪ 16 መርከቦችን ለመግዛት መታቀዱን ጠቁመው ÷ በተያዘው ዓመት ብቻ ስድስት መርከቦች ይገዛሉ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን መርከቦች ጨምሮ በቻርተር ከ70 በላይ መርከቦችን በመጠቀም 370 በሚደርሱ ወደቦች ላይ ተደራሽ በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡
ኢባትሎ የኢትዮጵየን ወጪ እና ገቢ ንግድ በማሳለጥ ለሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ያለውን ድርሻ ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ መርከቦች በሚንቀሳቀሱባቸው ቀጣናዎች የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሀገሪቱን እያስተዋወቁ እንደሚገኙም አውስተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ