የሀገር ውስጥ ዜና

“የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎች” የሚለው መጽሐፍ የኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ማሳያ ነው – ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ

By Mikias Ayele

February 20, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) “የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎች” በሚል ርዕስ የተጻፈው መጽሐፍ ከአባቶች የተወረሰ የኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ማሳያ ነው አሉ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ።

በልዩ ዘመቻዎች ዕዝ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥነው ”የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎች” በሚል ርዕስ የተፃፈው መጽሐፍ ዛሬ በሀዋሳ ተመርቋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ በመጽሐፉ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሠራዊቱን ታሪክና የግዳጅ አፈፃፀም የመሰነድ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

መጽሐፉ የክፍሉን ታሪክ ከምስረታው ጀምሮ የዳሰሰና በተጨባጭ እውነት ላይ ማተኮሩን ጠቅሰው፤ በመጽሐፉ ውስጥ የተቀመጡት የተለያዩ ታሪኮች ብቻቸውን ብዙ መጽሐፍት እንደሚወጣቸው ጠቁመዋል።

“የውጊያ ማርሽ ቀያሪዎች” የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች እና የክፍሉ አባላት ያላቸውን ጥልቅ ወታደራዊ ዕውቀትና ልምድ ለመፃፍ መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ለታሪክ ምሁራን ማጣቀሻነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥረው ይህ መጽሐፍ ከአባቶች የተወረሰ የኢትዮጵያዊያን ጀግንንት ማሳያ ነው ብለዋል።

ዕዙ ያስመዘገባቸውን ድሎች አጠናክሮ ለማስቀጠል የበለጠ መዘጋጀት እንደሚገባም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስገንዝበዋል።

የዕዙ የአሸናፊነት ሚስጥር ያልተቋረጠ ዝግጅት በመሆኑ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ማሳሰባቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል ገልጿል።