አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዋና አሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል፡፡
በስልጠና መድረኩ የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ÷ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ እንዲሆን የምርጫ አስፈጻሚዎች ሚና የማይተካ ነው ብለዋል፡፡
ብቁ እና በሕግ መሰረት የሚሰሩ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለማብቃት ደግሞ የዋና አሰልጣኞች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ዋና አሰልጣኞቹ የሚያገኙትን ስልጠና በትኩረት እና በኃላፊነት ስሜት ለመስክ አሰልጣኞች ማስጨበጥ እንደሚጠበቅባቸው አመላክተዋል።
በስልጠናው 300 የሚሆኑት ዋና አሰልጣኞች እየተሳተፉ ሲሆን በማንዋል እና በቴክኖሎጂ የታገዘው የመራጮች ምዝገባ በምን አይነት መልኩ መከናወን እንዳለበት የክህሎት ስልጠናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡
ከስልጠናው በኋላ ዋና አሰልጣኞቹ ከ5 ሺህ በላይ የመስክ አሰልጣኞችን የሚያሰለጥኑ ሲሆን፤ የመስክ አሰልጣኞች ደግሞ በተዋረድ ከ214 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ሥልጠና ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።