የሀገር ውስጥ ዜና

ትኩረት በማግኘቱ ትርጉም ያለው ለውጥ ያስመዘገበው ግብርና …

By sosina alemayehu

February 21, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስቴር መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት ትርጉም ያለው ለውጥ እየተመዘገበ ነው አለ።

ሚኒስቴሩ፣ ከአማራ ክልል የግብርና ቢሮ፣ መሬት ቢሮ እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የግብርና ኢንቨስትመንት ፎረም ተካሂዷል።

በፎረሙ ላይ የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ግብርናውን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።

በግብርና ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በመመለስ በተሰራው ስራ የባለሃብቱን አስተዋጽኦ ማሳደግ መቻሉን ገልጸው፤ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ባለሀብቶችን በመደገፍ የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ተደርጓል ብለዋል።

የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ሀላፊ አዳነ መሀሪ (ዶ/ር) በበኩላቸው የባለሃብቱን ተሳትፎ ማሳደግ በመቻሉ ገበያ ከማረጋጋት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

የክልሉ መንግሥት በግብርና ዘርፍ ለሚሰሩ ባለሀብቶች መሬት እያቀረበ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አፀደወይን (ዶ/ር)፤ ተቋማቸው ጥናትና ምርምር በማድረግ የግብርና ዘርፍን እየደገፈ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የተሻለ ምርት የሚሰጡ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ እንደሆነ ገልጸው፤ በእንስሳት ሀብት ልማት ላይም ምርታማነትን የሚያሳድጉ ተግባራት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በምናለ አየነው