አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስክ ተሰማርተው መሥራት ይችላሉ አሉ።
‘አካል ጉዳተኝነትን የሚያካትት ማህበረሰብ ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት’ በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም ለ34ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ በወላይታ ሶዶ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።
አቶ አባይነህ ጉጆ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስክ እንደማንኛውም ዜጋ መሥራት የሚችሉ እና ውጤት የሚያመጡ ናቸው።
ነገር ግን በአንዳንድ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ አካል ጉዳተኝነትን ካለመቻል ጋር የማያያዝ የተሳሳተ አመለካከት መኖሩን ገልጸው፤ ይህንን የተሳሳተ አመለካከት ለመፍታት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አካል ጉዳተኞች በሁሉም መስክ ተሰማርተው በመሥራት እና ውጤት ማምጣት የሚችሉ መሆናቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ደነቀ ዳጮ በበኩላቸው፤ ለአካል ጉዳተኞች ተገቢው ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ተናግረዋል።
አካል ጉዳተኛ የሆኑ ግለሰቦች ጠቃሚ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ላይ በመሳተፍ አለመቻል የሚለውን የተሳሳተ አመለካከት እየቀየሩ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ካሰች ኤልያስ አካል ጉዳተኞች በተለያዩ የሥራ ዕድል ፈጠራዎች ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።
የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ለማሳደግ መሰራት እንዳለበት ገልጸው፤ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳይ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይገባል ነው ያሉት።
በአበበች ኬሻሞ