አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ትምህርት በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ግጭቶችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ከፍተኛ ሚና አለው አሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ጌትነት ታደለ (ፕ/ር)።
ተመራማሪው ከፋና ፖድካስት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ትምህርት በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መሰረት ሊሆን የሚችል መሆኑን አንስተዋል፡፡
እንደ ሀገር ለመለወጥ ትምህርት ላይ መስራት እንደሚጠበቅ አስረድተው÷ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎችም ይህንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የተማረ ሰው በየትኛውም ዘርፍ ቢሰማራ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚችል ጠቅሰው÷ አሁን ላይ እንደ ሀገር የሚስተዋሉ ችግሮች የባለፉት ጥቂት ዓመታት የተበላሸ የትምህርት ሥርዓት ችግሮች ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
በመነጋገር የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ትምህርት ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
እንደ ሀገር የትምህርት ተደራሽነት ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራም ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች አሁንም ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በብርሃኑ አበራ