የሀገር ውስጥ ዜና

ሐዋሳ አፈጣጠሯ ውብ፣ ሰዎቹ ውበትን መስራትና መልሶ መጠበቅ የሚችሉ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

February 22, 2026

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሐዋሳ አፈጣጠሯ ውብ፣ ሰዎቹ ውበትን መስራት እና መልሶ መጠበቅ የሚችሉ ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብላቴ ወንዝ ሰፋፊ የፍራፍሬ ልማት ስራን በተመለከቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ በሐዋሳ እየተሰራ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ሐዋሳ አፈጣጠሯ በጣም ውብ ነው፤ ሰዎቹ ውበትን መስራትና መልሶ መጠበቅ የሚችሉ ናቸው በማለት ገልጸው÷ ከተማዋ ላይ ያየነው አስደማሚ ውበት ተጠናክሮ ከቀጠለ እና ከሰፋ ምን ያህል የቱሪስት መስህብ መሆን እንደሚችል ያሳየ ነው ብለዋል።

የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የክልሉ መንግሥት አጠቃላይ በሚያደርገው ድጋፍ ከተማዋን መልሶ አስውቦ መስራት ላይ በጣም ተስፋ ሰጪ ጅማሮ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እየተመረቱ ከሚገኙ የሶላር ምርቶች በሚቀጥለው ዓመት ከግማሽ ቢሊየን ዶላር በላይ ኤክስፖርት እንደሚደረጉ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ከአዲስ አበባ እስከ ሐዋሳ ያለው የዋና መንገድ ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው÷ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ከሐዋሳ አዲስ አበባ ለመጓዝ ቢበዛ 2 ሰዓት እንደሚሆን አመልክተዋል።

በዮናስ ጌትነት